Skip Navigation Links    
     





 

 
በደቡብ ክልል በሁምቦ ወረዳ የሰባት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ነዋሪዎች ከካርቦን ልቀት ካሳ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተጠቃሚ ሆኑ

Monday, February 08, 2010

 
     
   

 አዲስ አበባ የካቲት 1/2002(ሬዲዮ ፋና) የኢፌዲሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መስፍን እንዳሉት በወረዳው የሚገኙት የሰባት ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ነዋሪዎች የገንዘቡ ተጠቃሚ የሆኑት በ2 ሺህ 728 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ደን 165 ሺህ ቶን ካርቦን የመምጠጥ አቅም እዳለው በመረጋገጡ ነው፡፡

 

የሰባቱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከካርቦን ልቀቱ በተገኘው ካሳ ተጠቃሚ የሆኑት እ.ኤ.አ.1990 ዓ/ም በአካባቢያቸው የተራቆተውን መሬት በደን በማልማትና በመንከባከባቸው በባለሞያዎች በተደረገ ጥናት ደኑ የካርቦን ልቀትን የመምጠጥ አቅም አለው፡፡

 

ከበለጸጉት አገሮች ከሚሰጠው ገንዝብም ለመጀመሪያ ጊዜ 726 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ክፍያ እንደሚለቀቅላቸውና ገንዘቡ ነዋሪዎቹ ተከፋፍለው የሚወስዱት ሳይሆን በእቅድ ላስቀመጡት እንደ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ መንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ አገልግሎት የሚውል እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

 

በሁምቦ ወረዳ ደኑ በመልማቱ በአካባቢው ይፈጠር የነበረውን የመሬት መሸርሸር መቅረቱን፣ ደርቀው የነበሩ ምንጮች እንደገና አገግመው ውሃ በማፍለቃቸው በአካባቢው የሚገኙ ወንዞች በውሃ መሞላታቸውንና አካባቢው በመራቆቱ ምክንያት ጠፍተው የነበሩ የብዝሃ ህይወት ሃብቶች በአዲስ መልክ እያቆጠቆጡ መምጣታቸውን አቶ ደሳለኝ አመልክተዋል፡፡

 

እንዲሁም በደኑ ውስጥ የኤኮ ቱሪዝም በማልማትና በመጠቀም፣ በዛፎቹ የንብ ቀፎዎችን በመስቀልና  ማር በማምረት ለነዋሪዎቹ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸቱን ነው አቶ ደሳለኝ የተናገሩት፡፡

 

የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን ከሚያገኙት የካርቦን ልቀት ካሳ በተጨማሪ ከ12 አመት በኋላ የደኑን ግማሽ ቆርጠው በመሸጥ ከአንድ ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ አደሚያገኙም ተናግረዋል፡፡

 

ቀሪውን የደን ሃብትም ከ10 አመት በኋላ ቆርጠው መሸጥ እንደሚችሉ ምከትል ዋና ደይረክተሩ ጠቁመው ከዚህ ሌላ ደን ቢያለሙ ለተጨማሪ ካርቦን ሽያጩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

 

ኢትዮጵያ በዓለም ያለውን የካርቦን ልቀት ባላት አቅም ለመከላከል ቆርጣ የተነሳች አገር እንደመሆኗ በሚሌኒየሙ የተጀመረው የደን ተከላ ፕሮግራም ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም ሕብረተሰቡ በየአካባቢው የተተከለውን ደን በመንከባከብና በመጠበቅ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

 

የግብርና ሚኒስቴርም ደንን በማልማት የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣትና የሁምቦ አካባቢ የሰባት ቀበሌዎች ተሞክሮና ያገኙት ጥቅም ለሌሎች አካባቢዎች በአስተማሪነት በመውሰድ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የራሱን ፕሮግራም አውጥቶ እንዲሰራ አስገንዝበዋል፡፡

 

የወረዳ ነዋሪዎች ደኑን ማልማት እንዲችሉ ወርልድ ቪዥን፣ የዓለም ባንክ፣ የጃፓን መንግስትና ሌሎችም ድጋፍ ያደረጉላቸው መሆኑን አቶ ደሳለኝ አስታውሰዋል፡፡